የኦሮሚያው ሰልፍ ምንጩ ስጋት ነው፤ የሰልፉ አላማ ያሉትና እውነታው የሰማይና የምድር ያህል ነው።
MerejaApr 3, 2023Read original
የኦሮሚያው ሰልፍ!
1) ላይ ላዩን ስለ “ለውጡ” ቢመስልም በዋነኛነት ግን ሰልፉ የተደረገው በስጋት ነው። ገና በአምስት አመት “ልቀቁ አሉን” የሚል ፍርሃት ያስደረገው እንጅ ለውጡ መጣበት የተባለው ቀንም ተረስቶ ነበር። መቸ እናድርግ ሲሉ አጋጣሚ ተገጣጥሞላቸው ነው የሚመስለው። ስልጣንን በስራና በመርህ ማስቀጠል ሲያቅት በሰልፍ የሚደግፈን ህዝብኮ አለ የሚል ማስታወሻ ቢጤ ይመስላል። “መንግስቴ ተጠቃ ብሎ የሚመጣ ህዝብ አለ” እንዳሉት ነው። “ለውጡ” ጠብቦ ጠብቦ ጅማ ላይ ደመቅመቅ እያለ ነው።
2) የብልፅግና አባላት በየክልላቸው ማደረግ ያልቻሉት ሰልፍ የአንድ ክልል ብልፅግና የ”ለውጡ” ተጠቃሚ/ባለተራ እንደሆን የተገለፀበት ነው። ስልጣኑ፣ ከስልጣኑ የተገኘው ጥቅም የአንድ አካባቢ እንደሆነ ራሳቸው የመሰከሩበት ነው። የኦሮሚያ ክልል ሰልፉን ሲያደርግ ይህን ግልፅ አድርጎ እንደሚያሳይ እንኳን ረስቶት ይሆናል። አሊያም ምን ያመጣሉ ብሎ ይሆናል። ፈጣጣነቱን፣ ልዩ ጥቅምን፣ ባለተራነትን ለምደውት ይሆናል።
3) ስለ ኢትዮጵያዊነት የተወራበት ለውጥ የቡድንና የብሔርተኝነት ማስፈፀሚያ ስለመሆኑ ዛሬ የታዩ ምስሎች ይመሰክራሉ። የኦሮሚያ ሰልፎች የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ስለማይታይባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት ወደ ደቡብ ክልል ሲሄዱ በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ያሸበረቀ አቀባበልን የዛሬ ሰልፍ አስመስለው እነ ሽመልስ አብዲሳ ጭምር ተጠቅመውበታል።
4) የሰልፉ አላማ ያሉትና እውነታው የሰማይና የምድር ያህል ነው። ሰልፉ ስለህብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም እንደሆነ አውርተዋል። ቀበሌ፣ ወረዳና ዞን ያልወሰዱበት ክልል ግን የለም። ሁሉም አቤቱታ እያቀረበ ነው። ስለ ወንድማማችነት እያወሩ ነው። በለውጡ ወቅት ከፊት የነበሩት የአማራና የኦሮሞ ብልፅግና እንኳን ፊት ተነሳስተዋል። ስለ ፍትህ አውርተዋል። እውነታው ግን ሸገር በሚሉት ከተማ ንፁሃንን ቤታቸው ውስጥ እንደቀበሩት ፍትሕን በአናቷ ተክለዋታል። ስለ ሰልፉም ስለ ለውጡም የሚወራው በቦታው የለም።
5) በቀደም የትህነግ ሰዎች ጋር ሸብ ረብ እያሉ ነበር። ዛሬ ይህ ቀን ፍትሕ የተገኘበት፣ ሴራ የተቀበረችበት፣ ህዝባችን ከባርነት የተላቀበበት፣ ወዘተ ወዘተ ሲሉ ትህነግን በደንብ ሲያወግዙት ውለዋል። ጌታቸው ረዳ ከእነ ሽመልስ ጋር ሰንብቶ ገና ከራባቱን ሳያወልቅ ትህነግ የተገረሰሰበት ቀን ተብሎ ሲከበር ውሏል። የትህነግ አክቲቪስቶች ውጠዋት እንጅ እነሱ የካቲት 11 ደርግን ከሚረግሙት ያልተናነሰ ትህነግ ዛሬ ሲረገም ውሏል። ይበሉት! ያ ማለት ግን ትህነግን ያባረረው የኦሮሚያው ንቅናቄ ነው ማለት አይደለም። ግን “የለውጥ ኃይል” የተሰኘው ጋር ሆነው ተባረረ ያሉት ኃይል ጋር ሲዳሩ ሰንብተው፣ ከመንገድ ተመልሶ ላቡን ሳይጠርግ በስድብ አጥረግርገውታል። እንዲህ ግራ ግብት ያለው ነው ለውጡም ሰልፉም።
6) ሌላውን እንደታዛዥ ስለሚያዩት ሰሞኑን በሌሎቹ ክልሎች ሰልፍ አድርጉ ብለው ሊያዙ ይችላሉ። መጀመርያ ግን የራሳችን ነው ብለዋል። እንደ ስልጣኑ፣ እንደ ጥቅሙ።