“ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማዋቀር በሚደረገው ጥረት አፍራሽ ሚና በሚጫወቱ ላይ እርምጃ ይወሰዳል”
BBCApr 9, 2023Read original
9 ሚያዚያ 2023, 09:24 EAT
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ መከላከያ እና ሌሎች የፀጥታ አካላት ለማስገባት በሚያደርገው ጥረት ላይ አፍራሽ ሚና በሚጫወቱት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳል አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥታቸው የክልሎች ልዩ ኃይል አባላትን ወደ አገር መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ ወይም ወደ መደበኛ የክልል ፖሊስ ለማስገባት ሲዘጋጅ የቆየ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ የመንግሥት ተግባር ዙሪያ “ሆን ብለው የአፍራሽነት ሚና በሚጫወቱት ላይ ተገቢውን የሕግ ማስከበር እርምጃ ይወሰዳል። ለዚህም በቂ ዝግጅት ተደርጓል” ሲሉ የአስተዳደራቸውን ጠንከር ያለ አቋም ጠቅላይ ሚኒስተሩ አሳውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን የመንግሥታቸውን አቋም ይፋ ያደረጉበትን መግለጫ ዛሬ እሁድ ሚያዚያ 01/2015 ዓ.ም. በጽህፈት ቤታቸው በኩል ያወጡት፣ መንግሥት የክልሎችን ልዩ ኃይል መልሶ ለማደራጀት የያዘውን ዕቅድ በመቃወም በተለይ በአማራ ክልል ውጥረት በነገሰበት ወቅት ነው።
ባለፉት ቀናት “የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ትጥቅ አይፈታም” በሚል የተቃውሞ ሰልፎች በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ስለመካሄዳቸው ተዘግቧል።
የልዩ ኃይሎችን ወደ ሌሎች የፌደራል እና የክልል የመከላከያ እና የፀጥታ ተቋማት የማስገባቱ ዕቅድን አጥብቆ ከተቃወሙት መካከል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ አንዱ ነው።
የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር መልካሙ ሹምዬ፤ የአማራ ክልል ከውጭም ከውስጥም የፀጥታ ስጋት የተጋረጠበት ስለሆነ ውሳኔው ወቅቱን ያልጠበቀ እና ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ መልካሙ “ከአማራ ክልል ውጭ ልዩ ኃይሉን ትጥቅ ለማስፈታት እንቅስቃሴ የተጀመረበት ክልል የለም” ከማለታቸው በተጨማሪ፣ ልዩ ኃይሉን መልሶ በማደራጀቱ ላይ የፌደራሉም ሆነ የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ከል ዩ ኃይሉ ጋር ምንም ዓይነት ውይይት አላካሄዱም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን በመግለጫቸው ላይ ውይይቶች መካሄዳቸውን እና ውሳኔውም በሁሉም ክልል ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸው፤ አስተዳደራቸው የክልል ልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌላ መዋቅር ለማስገባት በሚያደርገው ጥረት የትኛውም አይነት ተቃውሞ ቢገጥመው ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
“ይህ ውሳኔም ለኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እና ለሕዝቡ ሰላም ሲባል ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን ተግባራዊ ይደረጋል” ብለዋል።
ልዩ ኃይሎች “ጊዜያዊ” እንጂ ዘለቄታዊ ጥቅም ስለሌላቸው ወደ ሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች ማስገባት አስፈልጓል፣ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አገሪቱ በክልል ልዩ ኃይሎች ምክንያት የአንድነት ስጋት ገጥሟት ነበር ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ከክልል ልዩ ኃይሎች ጋር በተያያዘ ከአንዴም ሁለት ጊዜ የአገርን ሉዓላዊነት እና አንድነት የተገዳደሩ ፈተናዎች ገጥመዋት እንደነበር አይዘነጋም። ከአንድነት እና ሉዓላዊነት ሥጋትነት በመለስም በክልሎች መካከል የማያስፈልግ ተፎካካሪነት እና ተገዳዳሪነት እንዲፈጠር መንስኤ ሲሆኑ እናያለን” ብለዋል።
“ከጊዜያዊ መፍትሄ ዘላቂ ጥቅም አይገኝም!”
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በመግለጫቸው የክልል ልዩ ኃይሎች ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ ጥቅም ለአገር ሊያስገኙ አይችሉም ብለዋል።
በማዕከላዊ የፀጥታ ተቋማት መመከት የማይቻል አጣዳፊ የፀጥታ ሥጋቶች በሚያጋጥሙበት ወቅት እንደ ሚሊሻ እና ልዩ ኃይል ያሉ ኃይሎች ሊደራጁ እንደሚችሉ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በጥድፊያ በጊዜያዊነት የተቋቋሙት ኃይሎች የሚሰጡትም ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ አይደለም ብለዋል።
ዘመናዊ ሠራዊት የሚለካው በብዛት ሳይሆን በጥራት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አሥር ቦታ ተበጣጥሶ ከተዋቀረ መቶ ሠራዊት ይልቅ በአንድ ማዕከል በሥርዓት የተደራጀ ሠላሳ ሠራዊት ይበልጥ ጠንካራ” ነው ብለዋል።
ልዩ ኃይሎችን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅር የማስገባት ዕቅድ
የልዩ ኃይል አባላትን ወደ መከላከያ፣ ወደ መደበኛ ፖሊስ ወይም ወደ ፌደራል ፖሊስ እንዲገቡ የማድረግ አጀንዳ ለረጅም ጊዜ ሲታሰብበት እና ሲመከርበት የቆየ ጉዳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሕዝብ ጋር በተደጋጋሚ በተደረጉ ውይይቶች “...ልዩ ኃይሎች ወ ደ መከላከያ እንዲጠቃለሉ ሕዝቡ ጠይቋል” ያሉ ሲሆን፣ መንግሥታቸውም ይህን ለመፈጸም ተገቢውን ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔው በሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ላይ የሚተገበር መሆኑን ገልጸው፤ “የእዚህ ወይም የዚያ ክልል ልዩ ኃይል ብቻውን ትጥቅ ሊፈታ ነው፤ የዚህኛው ክልል ይቆይ ተብሏል...የሚሉ ውዥንብሮችን የሚነዙ አካላት ገሚሶቹ ባለማወቅ ሲሆን፤ የተቀሩት ዓላማቸው ሕዝብ ከማበጣበጥ የዘለለ አይደለም” ያሉ ሲሆን፣ ውሳኔውን ከሚቃወሙት መካከል “ጥቂት የማይባሉት ከዚህ ቀደም የክልል ልዩ ኃይል መፍረስ አለበት ብለው ሲጽፉና ሲሞግቱ የከረሙ ናቸው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደራቸው የልዩ ኃይል አባላትን ትጥቅ የማስፈታት ዕቅድ እንደሌለው አስታውሰው፣ አባላቱ በሌላ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ገብተው የበለጠ ሥልጠና እና ትጥቅ አግኝተው አገርን በተሻለ ወደሚያገለግሉባቸው መዋቅሮች እንዲገቡ የሚያደርግ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ርብርብ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሎች ስር ተዋቅረው የቆዩት ልዩ ኃይሎችን በተመለከተ ጥያቄ እና ስጋት ሲቀርብ የነበረ ሲሆን፣ ክልሎች በሥልጣና እና በትጥቅ የተደራጀ ወታደራዊ ኃይል መገንባታቸው ሕገወጥ ነው ሲባል ቆይቷል።
ይህንን የክልሎችን ልዩ ኃይሎች መልሶ የማዋቀር እርምጃን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የተባሉት ፓርቲዎች የሚደግፉት መሆናቸውን ገልጸው መግለጫ ያወጡ ቢሆንም አፈጻጸሙ ላይ ግን ጥያቄ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ፌደራል እና ወደ የክልል የፀጥታ መዋቅር የማስገባት በጎ ጅምር መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን “አላስፈላጊ ውዥንብር ፈጥሮ ሌላ አገራዊ አደጋ እንዳይጋብዝ ጥንቃቄ ይፈልጋል” ብሏል።
የክልል ልዩ ኃይሎች በፌደራል መንግሥት የፀጥታ ዕዝ ሥር እንዲገቡ መደረጉ ተገቢም ልክም ነው ያለው ኢዜማ፣ “ውሳኔው ከመዘግየቱ በስተቀር ተገቢነቱ ላይ ጥያቄ ሊነሳበት አይገባም” በማለት፣ አተገባበሩ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚፈልግ እና ካለው “ሥር ከሰደደው የዘውግ ፖለቲካ ጡዘት አኳያ አፈጻጻሙ በተጠና መልኩ መኾን አለበት” ብሏል።
የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን መልሶ ከማዋቀር ጋር በተያያዘ መግለጫ ያወጣው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ እንደ ኢዜማ ሁሉ የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ፌደራል መንግሥት ወታደራዊ እና የፀጥታ አካላት ውስጥ እንዲካተቱ መደረጋቸውን ደግፏል።
“በመርኅ ደረጃ የክልል ልዩ ኃይል መፍረስ እንዳለበት እና በአገራዊ የመከላከያ ሠራዊት መጠናከር እንዳለበት” እንደሚያምን ገልጾ፣ ነገር ግን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር አሁን ተግባራዊ ማድረግ ግን ተቀባይነት የለውም ብሏል።
ጨምሮም የፌዴራል መንግሥት የአማራ ልዩ ኃይል “እንዲፈርስ ያስተላለፈውን ውሳኔ በሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ላይ በእኩል ደረጃ እና መጠን ተፈፃሚ የማይሆን በመሆኑ” ውሳኔውን ባልደራስ አጥብቆ እንደሚቃወመው ገልጿል።
የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የክልል ልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች የማካተት ሥራው በመላ አገሪቱ ባሉ ሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ የሚተገበር ነው።